0
<< ïðåäûäóùàÿ çàìåòêàñëåäóþùàÿ çàìåòêà >>
31 ìàðòà 2020
Dao De Ching Amharic

ዳው ዴ ጂንግ
(ru) Þëèÿ Ïîëåæàåâà http://lib.ru/POECHIN/lao5.txt
https://archive.org/details/20200331_20200331_1659/mode/2up
(es) https://skymon.binoniq.net/2020/10/28_1
(en) https://skymon.binoniq.net/2019/11/01_1
(ua) https://skymon.binoniq.net/2019/11/01
(he) https://skymon.binoniq.net/2019/10/31_1
(ar) https://skymon.binoniq.net/2020/01/04
(fa) https://skymon.binoniq.net/2020/01/31
(it) https://skymon.binoniq.net/2020/10/16_2
(de) https://skymon.binoniq.net/2021/01/05_1
(ur) https://skymon.binoniq.net/2021/02/27
(tr) https://skymon.binoniq.net/2021/03/15_2


ዳው ዴ ጂንግ Byuro Perekladiv «Myster Kronos» https://mk-translations.ua/ua/contacts-ua/

1

የዳውን እውነታ በቃላት ማስረዳት አይቻልም፣

የተነገረ ቃል ሁሉ — እውታ አይደለም።

ያለስያሜ ያለ — እንደስማይና መሬት ምስጢር ነው፣

ስያሜ ያለው ደግሞ — በገላጭ ቃል የተወለደ ነው።

ሁለቱም በአንድ ላይ፣ ፍጥረትና ስያሜ —

ህያው የጥልቅ ሀቅ ዘር ነው።

በስሜታዊነት መዘፈቅ፣ እንዳንችል ይሽፍነናል ለመረዳት ነገሮችን።

ከዚህ ስሜት ነጻ የሆነ ብቻ ያገኛል እውነታን፣

የሆነ ቅርጽ በማውጣት የተደበቀውን።

ከቃላት ወደ እውነታ — ወደተዓምር መንገድ።

2

የቅጽል ስምነት ጥያቄ ነው — ደግነትና ክፋት።

ስያሜ ከተሰጠው፣ እናበጅለታለንና በዚሁ መስፈርት።

ቁንጅና የሚኖረው፣ አስቀያሚነት ባለበት ብቻ ነው ለማወዳደር፣

ሞትንም እንዲሁ፣ ስንገነዘብ ነው ስላለመኖር።

ረጅምና አጭር የምናየው በንጽጽር ነውና፣

እጥረትን ስንረዳ — ርዝመትን ማወቅ እንገነዘባለንና።

ሙዚቃ እንዲጫወት መቀጠል አለበት ከዝማሬ ዝማሬ፣

መጀመሪያው መጨረሻ ነው ያለፈው ጅማሬ።

ስለዚህ ሳይንቀሳቀስ ጠቢብ ይፈጽማል፣

ያስተምራል በዝምታ ያለቃል፣

ለመስራት እንጂ፣ ለራስ ማድረግን አይጥርም፣

እና ሳይሳተፍ፣ እንደገና እንቅስቃሴን ይፈጥራል።

ለውጥን በማምጣት ያለትልቅ ጥረት፣

እና ባገኘውም ውጤት ባለመኩራራት፣

መቼውንም አይለየውም ፍቅርና ክቡርነት።

3

መቼም እውቀት ካላሰረጸብን መከበር —

ማን ስለራሱ እውነታ ይከራከር ነበር?

መቼም ቢሆን እምነት መኖሩን ባላሳጣን ነበር —

ማን ሌባ ይሆን ነበር ለውድ እቃ ሲባል?

መቼውንም የሚታይ ባልነበር የሚያሳስት ነገር፣

የሰዎችን ልብ የሚያማልል?

ስለዚህ ጠቢብ ሲጀምር መምራት፣

ይሞክራል ህዝቡን ማብላት ማጠጣት፣

ነጻነትን በማዳፈን፣ የመንቀፍ ፍላጎት ስሜትንም።

የሚያቅ ያውቃል ህዝብ አይነካም።

ይልቅ በስራው ህዝቡን ያመጣል ወደሰላም።

4

ቀላል አይደለም ዳውን ለመግለጽ።

ቅርጽ ሳይኖረው — የሆነው የሁሉ ፍጥረቶች ምንጭ።

ባንድ በኩል ባዶ — ግን በሌላ እንቅስቃሴ ነው የማያቋርጥ፣

ቅርጽ አልባ ነው — የቅርጾች ሁሉ መጀመሪያ።

ጥልቅ — የክስተት ሁሉ ምክንያት!

ተፈላጊ ነገር የለም፣ ባንጻሩ ሁሉም ጠቃሚ ነው።

ፍጥረታት ሁሉ — ትብያ ነው ካጠገብ ሲገኝ።

የዳው ሀብት፣ እውቀት፣ ጭንቀት

የሚወዳደር ነው ብቻ ከራሱ ከባዶነት።

እሱ — ቀጣይ ነው የጅምሮች ጀማሪ።

አላውቅም፣ ምን ወይም ማን እንደፈጠረው።

5

ሰማይም መሬትም በዝምታ ያያሉ ስቃይን።

የላትም ተፈጥሮ የሰብአዊነት ሚዛን፣

አይሰማትም ርህራሄ ለተበደሉት፣

መቀየርም ቢሆን የተፈጥሮን ሂደት።

ጠቢብ ህግን በመከተል የተፈጥሮን እንዲሁም፣

አይታየውም ለህዝቡ የፍትህ ጥቅም፣

የተፈጥሮአዊ ህይወትን አብልጦ በማየት።

የአንዳንድ እቃዎች አገልግሎት የሚወሰን ከሆነ በውስጣቸው ባዶነት፣

እንደ ቀጥቃጭ ወናፍ፣ ለምሳሌ፣ ወይም እንደ ዋሽንት፣

የበለጠ ባዶ ቦታ ሲኖር፣ የበለጠ ስራ ላይ ለማዋል አመቺ ነው፣

የበለጠ እንቅስቃሴ ሲኖር፣ የበለጠ ጠቃሚ ነው።

እንዲሁም በሰማይና ምድር መካከል ባዶ ቦታ ያለው፣

እንደ ዋሽንቱና ወናፉ አስደናቂ ነገር ነው።

ስለዚህ ብዙ ማለት ለምን ያስፈልጋል፣

በሁሉም ነገር ላይ መጠንን ማወቅ ያሻል።

6

የሰማይና መሬትን አመጣጥ ምንጭ ስንመረምር፣

በመጀመሪያ ላይ እናገኛለን በር፣

በርሱ ነውና ስር መሰረቱ ጥልቁ የመጀመሪያው ውልደት፣

ከሱ በኋላ — ባዶነት።

ከበሩ “ሊሆን ይችላል” ወይም ወደ በሩ “ነው”፣

የጥንቱ የማያቋርጠው የፈጣሪ ስራ፣

ከባዶነት — ወደማያቋርጥ የተለያየ ፍጥረታት መለወጥ፣

እንደ ክር፣ የተቀጣጠለ፣ መቼውንም የማያቋርጥ።

7

ብቻ በምክንያት ስለራሳቸው ሃሳብ የሌላቸው፣

ሰማይና መሬት ይኖራሉ ረጅም ዘመን።

ጠቢብም ሰው እንዲሁ ያደርጋል።

ረጅም እድሜ የኖረ፣ መኖርን የበለጠ ይወዳል።

ራሱ መጨረሻ መቆም የሚፈልግ፣ መጀመሪያ ይሆናል።

ማጣትን የማይፈራ፣ ደስታን ያገኛል።

የማይጨነቅ ስለራሱ፣ አትለውጠውም እድሉ።

8

ውሃ፣ ታላቅ ምሳሌ ይሰጠናል የኩራትን፣

ጥቅም የሚሰጥ ለሁሉም፣ እራሱ ፈላጊ ሰላምን፣

የበላይ ለመሆንና በማን አለብኝ ባይነት የማይታገል ከማንም፣

ትንሽ ቦታ የሚያረካው፣ በመንጋው የተጠላም።

እንደ ዳው መንገድ፣ እንደ አካሄዱ።

እንዲሁም ጠቢብ — ልቡ እንደመራው በክብር ይጓዛል፣

ከሁሉም ጋር በስምምነትና በጠባብ ቤት ይኖራ፣

ንግግሩ እውነታን ያዘለ፣ ህዝቡን በሰላም ይመራል፣

በጊዜው ይወስናል፣ የሚችለውን ጉዳይ ብቻ ይፈጽማል።

እንደ ውሃ ለሁሉም ቦታውን እየለቀቀ፣ ለሰላም ይጥራል፣

ስለዚህ ስህተትና መከራ አያልፉም ባጠገቡ።

9

መቼ ማቆም እንዳለብህ ማወቅ ግዴታ ነው።

ብርጭቆን ከጫፉ በላይ አይቻልም መሙላት፣

እንዲሁም አይቻልም መጠበቅ ትልቅን ሃብት፣

ስል ሰይፍ ይደንዛል ቀድሞ፣

በሀብት ወይም በስልጣን መመካት —

ነው መከራን ወደቤት ማስገባት።

ጉዳይህን ስትጨርስ መውጣት እወቅበት።

ይህ መንገድ ብቻ ነው የተፈጥሮ ህግጋት።

10

ከራስህ ከታረቅህ

ከስጋህና ከነፍስህ፣

አትችልም ልታጣው ማንነትህን፣

ከገራኸው ፍላጎትህን፣

መሆን ትችላለህ እንደ ጨቅላ ህጻን፣

ካጸዳህ መንፈስህን፣

መራቅ ትችላለህ ስህተቶችን፣

ያለማስመሰል በመውደድ ህዝቡን፣

በሃገሩ ላይ ከተሰጠህ ስልጣን፣

ትችላለህ መምራት ያለብልጠት፣

ከቻልክ፣ እንደ ህያው እናት፣

ህይወትና ሞትን በመቀበል ያለማወላወል፣

አትችልም ልታጣት ሰላምን፣

ማወቅ ከቻልክ ዓለም መላውን፣

ተንከባከብ፣ ተማር እና ተጨነቅ፣ ስትፈጥር፣

እና አድርግ፣ ሳይኖርህ፣

ስራ፣ ሳትጠብቅ ሽልማት፣

ግዛ፣ ሳትቀበል መከበርን —

እንዲህ ታውቀዋለህ የዴን በረከት።

11

ምን ያደርጋል ከሌለው ቀዳዳ፣ የእንዝርት ማሽከርከሪያ ክቡ እንጨት?

እራሱም ከሸክላ የተሰራ ገንቦ፣ ግን ጠቃሚ ነው የውስጡ ባዶነት፣

መጠኑም ከሰፋ ቤት ይኖረዋል የበጠ ምቾት።

ብዙ ጊዜ እንዲህ ባዶነት ይፈጥራል ጠቀሜታን፣

በመሙላት — ገቢን።

12

አይንን ያዳክማል የቀላማት ብዛት፣

ያደነቁራልም የድምጽ ጉላት፣

የተለያዩ ጣዕሞች ያደነዝዛሉ የመቅመስ ችሎታን፣

የማይረባም ልብ ይጭራል ቧልትን።

አልጠግብ ባይነት ሰላማዊ ኑሮን ያደፈርሳል፣

ጌጣጌጥም ወንጀልን ያጭራል።

ነገር ግን በነዚህ ከንቱ ነገሮች ያጓጉታል ጠቢብን፣

እሱ ስለመብሉ ይመርጣል ማሰቡን።

13

ርግማንም ሙገሳም ያስፈሩናል ሁለቱ፣

በራስህ የበለጠ እየኮራህ በመጣህ ቁጥር፣ ይጨምራል የበለጠ ፍርሃቱ።

መስሎ ያስፈራኻል፣ የሚጠፋ በሙገሳ፣ በክብር ቦታ ስታስቀምጥ እራስህን፣

ያስፈሩኻል ሰዎች ስታሳድድ እሱን።

እራስህን ስታቀርብ ቀለል አርገህ፣

አትፈራም ምን ይሉኛል ሰዎች ብለህ።

ስለዚህ በራስህ ዕይታ ራስህን ከዓለም አስበልጠህ፣

የከረረ ይሆናል በሷ ላይ ጥገኝነትህ፣

ከዚያም ለሰዎች ስታስተምር ጎደሎነት የዓለምን፣

ስትወዳትና እንዳመጣጧ ስትቀበላት ህይወትን፣

እምነት ታገኛለህ የሰዎችን።

14

የዳውን ትምህርት የስሜታችን ጫፍ ከተረዳው፣ ውስን ያደርገናል፦

መስማት አይቻልም እሱን — ከቃላት በላይ ነውና፣

ማየት አይቻልም እሱን — ከዕይታ ውጭ ነውና፣

መዳሰስ አይቻልም እሱን — በዳሰሳ ስሜታችን የማይታወቅ ነውና፤

በአንድ ላይ ቢሆን፣ ምን እንደሆነ አይታወቅም፣

ሳይንስ በደረሰበት መተንተን አይችለውም።

የሱ መነሳት አያመጣም ብርሃን፣

የሱ መውደቅ አይፈጥርም ጨለማን፣

ያ ስም የለሹ ዘላለም የሚኖር

እና ሁሌም ይመለሳል ወዳለመኖር፣

ያለቅርፅ ቅርፅ ያለው፣ አኗኗር፣ ግን ይዘት የሌለው፣

ግልጽ አይደለም፣ ስውር፣ በስያሜው ለመረዳት አስቸጋሪ ነው።

ከፊትለፊቱ የሚቆም — መልኩን አያየውም፣

የሚከተለው — ዱካውን አያገኘውም።

ህጉ ሁሌም ያዋህዳል

የሚከተለው ሰው ሁሌም እንዳገኘው ነው

እና የዓለም መጀመሪያ ምንጭ መሆኑን ያውቀዋል።

ይህን ህግ ዘላለማዊ የዳው ሰንሰለት ይሉታል።


15

ያኔ ጥንት የዳው ተከታዮች በጥልቀት ተረድተውት ነበር፣ የክስተትን ምንነት፣

ስለሆነም ለተራ ሰው ይከብደዋል እነሱን መረዳት።

ስለዚህ መተረክ ብቻ ነው የምችለው

የነሱን ምግባር፣

የውስጥ ዓለማቸው በውጫዊው ተግባር የተንጸባረቀበትን።

እንዲህ በጥንቃቄ ሲጓዙ በህይወታቸው፣

ልክ፣ ውሃ ላይ ተነጣጥለው የሚንሳፈፉ የበረዶ ቁራጮች በኩል አድርገው፣

እና እንዲህ በጥርጣሬና ተጠባብቀው ሲሄዱ፣

ልክ ከአሁን አሁን ያደፈጠ ጠላት አደጋ ይመስላል ሊጥልባቸው።

የዋህ ናቸው፣ ልክ እንደተራ ዛፍ፣

በስርዓት ተኮፍሰው፣ ልክ በእንግድነት እንዳሉ፣

ልክ እንደ ፀደይ በረዶ፣ ወደመሯቸው የሚመሩ፣

ቅን፣ ልክ እንደ አንባ እንግዳ እንደሚጠብቅ፣

ልክ ከተራራ እንደሚወርድ ናዳ፣ የማይበገሩ።

ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ እያለ እነሱን፣

እንደነገሩ የመግለጽ ችሎታ ነበራቸው፣ እነሱ ሁሉም፣

እና፣ እራሳቸው ባለመተግበር ውስጥ ሆነው፣

ሌሎችን ግን ወደ ሚሳካ ቅልጥፍና ያነሳሳሉ።

ዳውን በጣም ይከተሉ ነበር

ቁጥብ ነበሩ በፍላጎታቸው።

ባላቸው በትንሹ ረክተው፣

ከኑሯቸው ጋር ታርቀው፣

ግን አልፈጠሩም አዲስ ነገር።

16

አዕምሮዬን በሰላማዊ እረፍት ጠብቄ፣

ከባዶነት ጫፍ እደርሳለሁ።

እና እንዲሁ በዝምታ እታዘባለሁ፣

ከድቅድቅ ጨለማ ነገሮች፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ህይወት እያበሩ፣

እንደገና ወደ ራሳቸው መጀመሪያ ቀስ በቀስ ሲመለሱ።

ወደ ሰላምና እረፍትና —

እድል ለሁሉም ትመለሳለች ሳትለወጥ።

እንደ ውሃ አዙሪት የዚህ ዘላለማዊ ታላቅ ድርጊት

ይሉታል የጽናት ህግ።

እሱን ማወቅ ይወስዳል ወደ አዕምሮ ብሩህነት፣

የማይቀበሉትን — ይገፋፋል ወደ ክፋት።

የተቀበለው ጽኑነትን ይገነዘባል

በውስጡ ፍትሃዊ የተፈጥሮን ነጸብራቅ።

ህገ አምላክ፣ አለማችንን የሚመራው —

ብቸኛ፣ መቼውንም ለማጥፋት የማይቻል ኃይል፦

ያለ አካል፣ የተጋለጠው ለሞትና ለመከራ፣

ዘላለም ዳው ህይወቱን ያረዝማል።

17

ማግኘት አይችልም እምነትን፣

የራሱን ህዝብ የማያምን፣

ይመራል መጥፎ ከሁሉም

እና ይንቁታል ሰዎች አይወዱትም።

ስኬት ይኖረዋል የሌለው ወደር፣

በሁሉም ላይ ፍርኻት የሚያሳድር፣

ይደረሳል ትልቅ ቦታ

ካለ ፍቅርና ክብር።

መሪ ማለት ታላቅ፣

ማንነቱ በውል የማይታወቅ፣

በየጊዜው ለንግግር ብቅ የማይል —

እሱ ግቡን ይመታል፣

ሰዎች በአንድ ላይ ያስባሉ፣

ነገሮች ሁሉ በራሳቸው ይሄዳሉ።

18

ሰዎች በውስጣቸው ዳውን በሚያጡበት ጊዜ፣

ህብረተሰቡ በውጫዊ ህግ ይገዛቸዋል።

ሰው መኖር ባልቻለበት ጊዜ በይሉኝታ፣

በፊቱ ይደቀንበታል የዜግነትና የቤተሰብ ግዴታ።

ከውስጥ እምነቱጋ እና አእምሮው ከሚፈጥረው፣

ይመጣሉ ማስመሰልና ቸልተኝነት አብረው።

እርስ በእርሳቸው በሚጋጩ ቤተሰብ ውስጥም

በየጊዜው በንግግራቸው ስለ ግዴታ ያወሳሉ፣

የበለጠ ታማኝነትንና ታዛዥነትን ይጠብቃሉ።

እንዲሁም ግርግር በበዛበት ሃገር ውስጥም።

19

እውቀትና ፈጠራ ባይኖር፣

ሰዎች መቶ ጊዜ በበለጠ፣ ደስተኛ በሆኑ ነበር።

ባለሙያዎች ባይኖሩ፣ ውድ ነገር የሚሰሩ፣

ከፍተኛ ትርፍ ፈላጊ ነጋዴዎች ባልኖሩ፣

ምክንያትም ባልሆነ ለወንጀል።

ፍትህ፣ ሞራልና የመሳሰሉት ዕቀባዎች ባልነበሩ፣

እንደሚስማማ አድርጎ ለሁሉም፣ መንግስት ቢጥር ኖሮ፣

ሰዉ በተመለሰ ነበር፣ ወደሰላማዊው የቤተሰብ ኑሮ።

እነዚህ ሁሉ ምሳሌዎች የሚናገሩትን፣

መግለጽ እችላለሁ በአንድ አስተማሪ ቃል፤

ለጠቢብ፦

በህይወት ውስጥ እራስን ቀለል አድርጎ ማቅረብና፦

አለማስመሰል

ቁራጭ እንጨትና ንጹህ ብሩሽ።

ጠቢብ እራስ ወዳድነትን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ አለበት፣

እና እንቢ ማለት የራስን ፍላጎትና ጥረት።


20

ዛሬም፣ በየትኛውም ዘመን፣

ጠቢብ ያውቀዋል ከልቡ፣ ሃዘንን፣

ረጅም ነው ወይ መንገዱ፣ ከመወደድ ወደ መጠላት የሚወስደው?

እንዲሁም ይታያል ወይ፣ በክፋትና ደግነት መሃል ልዩነታቸው?

መፍራት ያለበት ሰው፣ ፍርሃትና ብስጭት የሚጠራ ነው።

በበአል መኻል ለብቻዬ የምደርስበት አጥቼ እየዞርኩ፣

ቀልብ የሚስብ ነገር እየመረጥኩ፣

እንደጨቅላ ህጻን ዓለምን በግርምት እያየሁ፣

ሳልፈልግ ከሰዎች ጋር ማውራት፣

ቤቱ የት ነው ያለው፣ ሰላም ማግኘት የምችልበት?

ተስፋ የለኝ እሱን ለማግኘት!

በወራጅ ውሃ እዋኛለሁ ልክ እንደ ጭራሮ…

ማካበት ከሆነ፣ የሁሉም ድካም ሃብትን፣

እቀራለሁ ፈንጠር ብዬ ብቻዬን።

ሞኝ! የሚታይ ስኬት የሌለኝ፣

በኔነቴ ያያሉ ሁሉም፣ ተራነት ምን መሆኑን።

አንዶቹ ስለሌሎች፣ የራሳቸው አመለካከት አላቸው፣

የሚተማመኑ፣ ምንም ጥርጥር የሌላቸው —

እና እኔ ብቻ በድቅድቅ ጨለማ እማስናለሁ።

የማይገባኝ! ከንቱ ስወለድም!

ሌሎች የሚረዱትን ለኔ ግልጽ አይደለም፣

እዋልላለሁ በጨካኙ አለም ልክ እንደ ህልም።

ሰዎች ሁሉ በችሎታቸው አሸብርቀው ይደምቃሉ፣

ወደ ግባቸው ለመድረስ በስራቸው ስኬትን ይሻሉ፣

እኔ ብቻ ነኝ አላማ የሌለኝ ልክ እንደ ማእበል

ንፋስ እያፏጨ እንደሚያነጉደው በባህር ላይ፣

አይመለከተኝም፣ የተለመደ የሰዎች ጭንቀት ጉዳይ፣

ከወላጅ — ተፈጥሮ እለጠፋለሁ ደረቷ ላይ።

21

የዴን ድንበር ዳው ይከልላል፣

የዴ ማንነት ከዳው ይወጣል፣

ግን እራሱ ዳው ትልቅ ምስጢር ነው።

ግልጽ ያልሆነ የማይታይ እንደ ምንነት፣

የእቃዎች ቅርጽ ተደብቆ በጭጋጉ ጥልቀት፣

በማይታየው ውስጥ ይገኛል ይዘት።

በድቅድቁ ጨለማ — የፍጥረታት ሽል፣

በውስጡ ይታያል የነሱ ጭላንጭል፣

የወደፊቱ እውነታ።

ከጥንት እስከ ዛሬ

አልተቋረጠም ጥረት

ግልጽ የሆነ ስያሜ ለመስጠት —

ያስፈልጋል የእውቀት መሳሪያ

ለነገሮች ሁሉ መጀመሪያ።

22

በብልሽት ውስጥ የመሻሻል ቅንጣት ነገር አለ፣

ጠማማ የነበር ይሆናል ቀጥ ያለ።

ባዶን ነገር ብቻ፣ ይቻላል መሙላት፣

መቆርቆዝ፣ አጋጣሚ ይፈጥራል ለእድሳት፣

የማግኘት እድል አለ ሁሌ በእጥረት፣

የማንኛው ነገር መትረፍረፍ — ያጋልጣል ለእጦት።

ተቃራኒ ነገሮች — አንድ ናቸው።

ይህ አመለካከት ነው
ጠቢብ የህይወቱ መርሆ አድርጎ ይቀበለዋል።
እና እሱ እዩኝ እዩኝ አይልም — ግን ይታያል፣
ለማሳመን አይደክምም — ማለት ግን እሱ ትክክል ነው፣
እራሱን አያሞግስም — መንገዱ ግን ሌሎችን ያስቀናል፣
ከማንም ጋር እራሱን አያወዳድርም —
እና ስለዚህ ብቁ ተፎካካሪ የለውም።

ትክክል አይደለም ወይ የድሮ አባባል፦
“በተበላሸ ሽል ውስጥ አለ ፍጹምነት”?
እንቅስቃሴን
ልክ ወደፍጹምነት መመለሻ አድርገህ ውሰደው።

23

አይቆይም ብዙ፣ የጠዋት ማዕበል፣

ሃይለኛ ዝናብም ቶሎ ያቋርጣል —

ተፈጥሮ ንግግሯን አታበዛም።

በተለይም፦

እራሱን ከተፈጥሮ ጋር ማወዳደር ለማይጥር፣

ልክ የምስታስጠነቅቅ ይመስል፣ መቆጠብን ለማስተማር፣

ስለዋና ነገር፣ ባጭሩ መናገር።

ህይወት ማለት ዳውን ማገልገል፣ ብሎ የሚያስብ ሰው፣

በትክክለኛ መንገድ ላይ ነው፦

ጉዞውም የተሳካ ይሆናል።

እንደ በጎ ምግባር አድርጎ የሚያስብ ህይወትን፣

ደግ ሰሪው እራሱ ይሆናል ነጸብራቅ —

ያገኛል በተራው፣ ከህይወት ደስታን።

በህይወቱ የማጣትን መንገድ ብቻ የሚያይ ሰው፣

በራሱ እጦት ጥፋተኛው እራሱ ነው —

ለዘላለሙም እንዳጣ ይኖራል።

ከዘመናት በኋላ ለሌሎች እንደ አርባ ቀን እድል ቆጥሮ ለመናገር።

እንደእምነቱ ለሁሉም የተሰጠ ነው።

24

በጣትህ ልቁም ብትል — አንድ ቦታ አትረጋም።

በረጅሙ ብትራመድ — ሩቅ አትደርስም።

እዩኝ እዩኝ ብለህ ብትደክም — ተቀባይነት የለህም።

እራስህን በራስህ ብታሞግስ — ክብር አታገኝም።

ሌሎችን በመዝለፍ — ስኬት አይኖርህም፣

እራስህን ከፍ አድርገህ በማየት — ለመሪነት አትበቃም።

ህያው ፍጡር ሁሉ ይሸሻል አላስፈላጊ ግርግር ።

አንተም ሽሽ — ከፈለግክ እንደ ዳው ለመኖር።

25

ዝብርቅርቅ ካለ ፍጹማዊ ነገር፣

መጀመሪያ ተፈጠሩ ሰማይና ምድር።

ጸጥታ፣ እንዲህ እንዲያ ከሌሎች የተነጠለ ነው!

እራሱን የቻለ እና የኖረ ሳይለወጥ፣

ዘላለም እየተለወጠ፣ ግን ምንም ሳይቀየር፣

በማንኛውም ሂደት ውስጥ እየገባ በጥልቀት

ሁሉንም ይፈጥራል።

ስሙን አላውቀውም፣

“ዳው” በሚል ምልክት አስቀምጠዋለሁ።

ካለብኝ ለሱ ስም መስጠት —

እሰይመዋለሁ ታላቅ ብቻ ብዬ።

ምን ማለት ነው ይህ ስያሜ?

ሰፊ በመሆኑ፣ ከአእምሮ ይጠፋል፣

ልክ የያዝኧው ሲመስል፣ ዋና ማንነቱ ግን እሩቅ ነው

ይሄ ነገር ወደአለመረዳት ይመልሰኛል።

እውቀትን ፍለጋ ይሄን ያህል ነው ወይ ረቂቅ፣

መድከም፣ እንዲህ ያለ ታላቅን ነገር ለማወቅ?

አዎ፣ ዳው መጨረሻ የለውም፣

እና ከዳው የሚወጡ፣ የስልጣን ህግጋት ማለቂያ የላቸውም፣

እና እነዚህ ህግጋት የሚመሩት አለም ፍጥረታት፣ ከመብዛታቸው ማቀፍ አይቻልም —

እና ቢሆንም እነሱን የማወቅ ፍላጎቱ በጣም ጠንካራ ነው እንደ ትኩስ ስሜት፣

አእምሮ የአለምን ፍጥረታት የማወቅ ችሎታ አለው

ከታላላቅ ኃይሎች መካከ የመጨረሻ ቦታ አይደለም የሚይዘው።

ፍጥረታትን በማወቅ የሰማይን ህግጋት ይገነዘባል፣

በዚህ መልኩ ዳውን ሊያገኝ ይችላል።

ከዘመን ዘመናት ይለፋል አእምሮ እየደጋገመ፦

“እኔ ፈጣሪ፣ እኔ ንጉስ፣ እኔ ሰው!”

26

ከባድ ስር፣ ቀላል እጽዋትን ይደግፋል፣

የሚያስጨንቀው —

የቅርንጫፎቹ ባለቤት የግንዱ እንቅስቃሴ፣

እና በንፋስ ጊዜ የነሱ ውዝዋዜ ደህንነት።

ጠቢብ በመንገዱ ላይ ተአምር ቢያገኝም፣

ከአላማው ፈቅ አይልም፣

ቁንጅናው ምንም ያህል ቢያብረቀርቅም፣

ሸክሙን በመጣል ወደዚያ አይሮጥም።

እንዲሁም ያገር መሪ መገንዘብ ያለበት፣

ዜጎቹን መናቅ እንደሌለበት።

የሱ ስልጣን ስር ይሰዳል፣ በህዝቡ ሰላም፣

ስሩ ከተነቀለ እንቅስቃሴው ሁሉ ዋጋ የለውም።

ለራሱ ብቻ ሲደክም፣ የሚወደውን ስኬት ዋጋ ያሳጣዋል፣

በማይረባ ግርግር፣ ስልጣን ለማጣት ብዙ ጊዜ አይወስድም።

27

ጥሩ ተጓዥ ማለት፣ ዱካ የማይተው ነው።

ንግግር አዋቂ፣ ንግግሩን መተንተን የማያስፈልገው ነው።

እቅድ ፍጹም የሚሆነው፣ ምንም አይነት እቅድ ከሌለ ነው።

ጠቢብ አንዱን ከአንዱ ሲያስር፣

ቋጠሮውን የሚያጠነክረው በገመድ አይደለም፣

ነገር ግን ቋጠሮው በሺ ዓመት አይፈታም።

ጠቢብ በሩን ቢዘጋም

ቁልፍና ጓጉንቸር አይጠቀምም፣

ነገር ግን በሩ ክፍት ቢሆንም ተስፋ የለም።

ስለዚህ ይኖራል ጠቢብ በሩን አድርጎ ክፍት፣

ሁሉንም ይቀበላል በእምነት፣

ለሚያንኳኳ ሁሉ በር ይከፈትለታል፣

ከችግር ጋር ይሁን፣ እምነት ባያሳድር፣

ማንኛውም ጸባይ ይኑረው፣ አውሬ እንኳን ቢሆን፣

እርዳታ ሳያገኝ፣ ማንም ከዚህ አይወጣም።

ስለዚህ ሁሌም ዝግጁ ነው ክፋትን ለማስጣል ፣

እራሱ ከማስተማር ሂደቱ ደስታ ያገኝበታል፣

ነገር ግን ከተማሪው ጋር ጠቢብ ግንኙነቱን አያጠብቅም

ማንኛው አይነት ቅርርብ ተጽዕኖ ያሳድራል ስለዚህ ይሸሻል፣

አያስፈልግም ማክበር መምህርን ከሚገባው በላይ።

28

ስትገነዘብ የራስህን ተፈጥሮ የወንድነት፣

የሴት ባህርይ በውስጥህ እንዳለ አያስፈልግም መርሳት።

ሜዳ መሆን አለብህ በሁለት ጋራዎች መሃል

ከሁለቱም በኋላ በመሆን፣

ትችላለህ ከዚያ መቀበል

ህይወትን እንዳለች እንደ ጨቅላ ህፃን።

ስታስብ ስለብርሃን

አትርሳ ጨለማ መኖሩን።

የትኛውም “ነው” “አይደለም” አለው፣

ማንኛውም አዎንታ በውስጡ ይደብቃል አሉታ፣

እያንዳንዱ ዱላ “ሁለት ጫፍ አለው” –

አንተም እራስህ የነዚህ ተቃራኒ ነገሮች ምሳሌ ነህ፣

እና የነሱን መኖር ሁሌም ከተረዳህ፣

ከብዙ ስህተቶች ልትተርፍ ትችላለህ።

ከዚያ እውቀትህ መጨረሻ እና ወሰን አይኖረውም።

ስለክብር ስታስብ ውርደት አትርሳ መኖሩን፣

በትዕቢትና ትህትና መካከል መተላለፊያ ሁን፣

በአንደኛውም ሁለተኛውም — ጫፍ፣ መቆም አይቻልም፣

የራስህን ክብር ትጠብቃለህ ከያዝክ ሁለቱንም፣

እንደልጥ በተፈጥሮው ከዛፍ ሊለይ እንደማይችል።

አንድን የዛፍ ግንድ፣ በመቁረጥና በመገዝገዝ፣

በጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።

እንዲሁም ጠቢብ በስራ ና ሃሳብ ያሉትን

ተቃራኒ ልዩነቶችን መጠቀም ይችላል።

ግን እውነታ ታላቅ እና አንድ ነው

እና መተነተንም መለያየትም አይችልም።

29

ልክ እንደሚስጥራዊ ዋንጫ አስደናቂ ነው ዓለማችን፣

ያዘለ በውስጡ ህይወታችንን ና እድላችንን፣

ምንም አይነት ኃይል አይገዛውም።

ዓለምን ለመግዛት የሚያስብ ሰው፣

ለመምራት፣ እንደፈለገው

ሁልጊዜ ለሽንፈትየተጋለጠ ነው።

ዓለም ሁልጊዜ ይገኛል በለውጥ ሂደት፣

ስለዚህ አስቸጋሪ ነው በአንድ ወጥ መምራት፣

ሲገዛ የኖረ መገዛት ሲጀምር፣

በነፃነት ሲተነፍስ የኖረ — ያጥረዋል አየር።

ኃይለኛ የነበር ደካማ ሊሆን ይችላል፣

ዛሬ የሚገነባ ነገ ይፈርሳል —

ስለዚህ ወራሪ የያዘውን ማጣቱ አይቀርም።

እና ብልህ ይህን ይገነዘባል፣

ከኔ በለይ በሚል ትዕቢት አይወጠርም፣

ከሚንቀለቀል ስሜታዊነት ና አክራሪነት እንዳስፈላጊነቱ ይርቃል።

30

ጠቢብ ለገዢ ሲሰጠው ምክር፣

ሂደትን መከተል እንደ ዳው አመራር።

የኃይልን እርምጃ መቼም አይደግፍም —

ሁልጊዜ መጥፎ ስራ ተመልሶ እራስን ያጠፋል።

ጦር ባለፈበት ቦታ ሙጃ ይበቅላል፣

ከጦርነት በኋላ

ዘመናት ያልፋሉ ለማስወገድ ድህነት ና ችግር።

ስለዚህ ብልህ ኃይልን

በፍላጎቱ አይደለም የሚመርጠው፣

ጠለቱ ወደዚያ ስገፋፋው ብቻ ነው፣

እናም ያሸንፋልም —

ዓላማውን ካሳካ ሌላ እርምጃ አይወስድም፣

ካሸነፈ በኋላ ወደ አጉል መኩራራት አይገባም።

ይርቃል ምርኮ፣ ዝናና ክብርን፣

አያገኝም ከዚህ ስኬት፣ ተጨማሪ ስልጣን።

እደዚህ ድል አድርጎ ከመጠን በላይ የሚበለጽግ

እና ብዙ ኃይል የሚያገኝ

ቶሎ ያረጅና ወዲያውኑ ይሞታል።

ዳውን የማይከተል መጨረሻው አሳዛኝ ይሆናል።

31

የጦር መሳርያ — ነው የክፋት ምልክት፣

መሳርያ ያመጣል ጥላቻና ፍርሃት፣

ይህ እንደ ቀኝ እጅ ይመሰላል፣

ዳውን ያገኘ በእጁ መሳርያ መያዝን ይጠላል።

ግራ እጅ ሲመራ ሰላምን ያሰፍናል፣

በሰላም ጊዜ፣ ጠቢብ ለንጉስ ምክር ይሰጣል፣

ግን በቀኙ፣ በሚጨፈጭፈው፣

ንጉስ ወደእልቂት ይገባል።

በሰላም ወቅት ግራ በክብር ይኖራል —

ቀኝ ግን የፈተና ወቅት ሲቃረብ የተከበረ ይሆናል።

እንዲህ ግራ የደጉን ዘመን ያስታውሳል፣

ቀኝ ግን የመከራ ጊዜ መዳረሻ ምልክት ይሆናል።

የጦር መሳርያ — የክፋት ምልክት፣

እና ይሄን ለድል መሪ የሚያነሳው፣

ምንም አይነት ምርጫ ሳይኖረው ሲቀር ነው።

ቢሆንም በትዕቢት አይወጠርም፣

በማሸነፉም ደስታ አይሰማውም።

እንዴት ሊደሰት ይችላል፣ የብዙ ሰው ሞት ምክንያት ሆኖ?

በዚህ የሚደሰትም ካለ፣ ህዝቡ አይረዳውም፣

ንጉስ ለድል በዓል ወታደራዊ ሰልፍ ሲቀበል፣

በቀኝ በኩል ከፍተኛ መኮንንኖች ይሰለፋሉ፣

በግራ በኩል ደግሞ ባለ ዝቅተኛ ማእረጎች ይቆማሉ።

የተመደበው የክብር ቦታ —

በጣም ክፋት የበዛበት ነው ይሄ ተርታ፣

በቀኝ በኩል የቀብርን ሰልፍ ያስታውሳል፦

የብዙ የጦር ሰለባዎችን መሪር ሀዘን ይጠራሉ —

ልክ እንደ ቀብር ሰልፍ፣ አሸናፊዎች ይቆማሉ።

32

ልክ እንደዛፍ ልጥ፣ ተፈጥሮ እና የዳው ምንነት

አይሰየምም እና በተለያየ ክፍል አይሰነጣጠቅም፣

እና ስለዚህ፣

በራሱ በትንሽ ምግባሩ እንኳ

በሆነ ነገር ውስጥ፣ ከየሁሉም ውህደት አንጻር፣

አይመደብም እንደ ታዛዥ ወይም ተቀጥላ —

እራሱ ለራሱ ታላቅ እኩያ ነው።

በንጉሱ ወይም ሌሎች ሹማምንቶች ቦታ

እንደዚህ ያለ መርሆ፣ በሰዎች ማህበረሰብ ውስጥ ማሰረጽ ቢቻል ኖሮ፣

ባልተፈጠረ ነበር የማስገደድ ፍላጎት፦

እንደራሱ በወሰደው ነበር ሁሉም የጋራን ጥቅም፣

እራሱን በራሱ በማስተዳደሩ ደስታ ያገኝ ነበር ህዝብ፣

ሩዝ ሳይሆን — በሰበሰበ ነበር የማር ዘለላ ከእርሻው፣

ይገጣጠሙ ነበር በመደነቅ መሬትና ሰማይም…

የሚያሳዝነው፣ ማለም ቆንጆ ነው —

ግን በከንቱ፣

እና ሰዎች የራሳቸው የሆነ ስርዓት አላቸው፣

የዚህ ስርዓት መሰረቱ — ክፍፍል፣

እና የተለያዩ ነገሮች ልዩነቶች ናቸው፣

የዚህ ሂደት ልዩነቶች ማስፈጸሚያ — ስያሜ ነው።

ስያሜ ያለው፣ ነገር ሁሉ፣ መገለጫ አለው፣

ሁሉም ይገኛል በሆነ ነገር፣ በንጽጽር ላይ ከሌሎች ጋር —

ልክ እንዳለው፣ በዛፍና ጣውላ መካከል፣

ለውበት ሲባል የተወለወለው፣

በምንነቶች መካከል ያለውን ልዩነት አሁን ይታያል።

ስያሜውችም፣ እንደ ልዩነቶች፣

በየቀኑ ለመጠቀም ምቹ ናቸው

እና በዚሁ የመጠቀሚያ ዋና መሳርያም ናቸው።

ግን የማጣት አደጋ አለው፣ አለምን በአንድ የማየትን፣

ስለዚህ የመፍጠር ድንበር ማወቅ ጠቃሚ ነው፣ አዳዲስ ቃላትን፦

በቃላት የተለያየ ሁሉ — በምንነቱ አንድ ነው።

የሆኑ ገባር ወንዞች በሸለቆ ውስጥ ይገሰግሳሉ፣

ግን ስታጤነው ወደባህር ነው የጋራ ጥረታቸው፣

ትረዳለህ፣ መለያየት እንደሌለ በፍሰቱ፣

ወጥ ውሃ፣ አንድ ነው።

እንዲሁም ዳው በእልፍ አእላፍ ምግባሩም

አንድ ሆኖ ይቀራል ለሁሌም።

33

በምትሃታው ኃይል በሰዎች አዕምሮ የሚመላለሰውን የምትረዳ ከሆነ — በጣም አዋቂ ነህ።

በልብህ ውስጥ ያለውን ጨለማ ክፍል የምትገነዘብ ከሆነ — መንፈስህ ብሩህ ነው።

በሌሎች ላይ አንተ የድል ጽዋን የቀመስክ ከሆነ — አንተ ታላቅ ጀግና ነህ።

ነገር ግን አንተ በእጥፍ ጀግና የምትሆነው፣ እራስህን መግራት ስትችልነው።

እራስህን መግራት ችለህ ደግሞ በስራህ የምትኮራ ከሆነ ደግሞ — አንተ ሃብታም ነህ።

የጥረት መንፈስ ካለህ አዳዲስ ስኬቶችን ለማግኘት ታታሪነት ይኖርኻል።

በረጅም መንገድ ላይ አላማህን ካልሳትክ፣ህይወትህ ለረጅም ጊዜ ትቆያለች።

ብትሞትም እንኳ፣ ከሰው አእምሮ አትፋቅም —

ሰውነትህን ባይሆንም፣ ያንተ መንፈስ ለዘመናት ይታወሳል።

34

እንደ የክረም ወንዝ ውሃ ሙላት የሚፈስ — ልክ እንደ ደው —

ወደ ቀኝ አይደለም ወይም ወደግራ፣ ወሰንም የለው፣ አቅጣጫም የለው።

እዚያ እልፍ አእላፍ ፍጥረታት፣ ሳያውቁ እንኳን ስለመኖሩ፣

ሁሉም ከእሱ ይወለዳሉ እና በድጋሚ ወደእሱ ይመለሳሉ፣

ፍጥረታትን ሁሉ ይፈጥራል፣ ምንም ሳይጠብቅ በተራው፣

የህይወት ኃይል እንዲኖራቸው፣ የዓለምን ፍጥረታት ይመግባል፣

ማንንም ሳያስገድድ እንዲሆን በስሩ።

የራሱየሆነ የሙከራ ጥረትም፣ ፍላጎትም የለውም።

በህብረተሰብ ውስጥ በአብዛኞው እንደሚታሰበው፣

እንደ ምስኪን ይቆጠራል የየዋህ መልክ እንኳን ያለው።

ግን ዳው፣ መርጦ መላውን ዓለም፣

ሁሉንም እንደገና ተቀብሎ፣ ሳይለይ ማንንም ከማን፣

እራሱን ሳይቆጥር እንደጌታም እንደታላቅም፣

ምሳሌ ይሰጠናል የታላቅነት ምንነት።

35

ተከትሎ የዳውን ምሳሌ፣ በመራቅ መከራን፣

ይጥራል ሁሉም ለመጓዝ ወደ ሰላም መንፈስ፣ ዘላለሙን።

ምግብና ደስታ ያለበት ቤት ብቻ፣

መቆየትን ይፈልጋል መንገደኛ።

በምግብ እንኳ፣ ዳው አይመሰልም፣

በመቅመስ፣ በማየት፣ በመስማት መለየት አይቻልም።

ግን በእሱ ውስጥ ደስታን ማግኘት የተማረ፦

በእርግጥ፣ ዝቆ አይጨርሰውም።

36

ለማጥበብ — መጀመርያ ማስፋት ያስፈልጋል፣

የሆነን ነገር ለማዳከም — የበለጠ ኃይል ስጠው፣ እንዲያበዛው፣

ብልጽግናን ስጠው — ማጥፋት ለምትፈልገው፣

ያለስስት ስጠው — ለመንጠቅ ካሰብከው —

ይኼው ነው ጥበቡ፣ ድክመቶችን በመጠቀም

ማሸነፍ ትችላለህ ማንኛውንም ኃይል።

37

ከድሮም ዳው ያለድርጊት ይኖራል፣

ግን ያልተሰሩ ጉዳዮችን ለበኋላ አያስቀምጥም።

ገዢዎች እንዲህ ማድረግ ቢችሉ፣

በራሱ መንገድ ይበለጽግ ነበር፣ አለም እራሱ።

ግን የሆነ ሰው ተፈጥሮአዊ ለውጥ የማይስማማው ከሆነ፣

ተጨማሪ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፣

አጠንክሮ ይህን ፍላጎቱ፣ ማስቆም ያስፈልጋል፣

ወድ ድንግል ተፈጥሮ እንዲመለስ በመጥራት።

ስም አልባዋ ንጹህ ተፈጥሮ በፍላጎ አትጠማም፣

በዚህ የተነሳ ታገኛለች እውነተኛ ሰላም።

የግል ፍላጎት አለመኖር — ወደሰላም ጉዞ ነው።

የዚያን ጊዜ ከጨረቃ በታች ስርአት ይነግስ ነበር።

38

መልካምነት የሚመነጨው ከንጹህ ልቦና ሲሆን፣

ሰዎች፣ እራሳቸውን ዝቅ አድርገው ለማሳየት ይጥራሉ።

የበለጠ ግብረ ገብ ሲኖረን፣

ያነሰ፣ የማስመሰልና ክፋት ስራ እንሰራለን።

በእንደዚህ አይነት አመለካከቶች አንጻር፣

ታዋቂ መልካም ምግባሮችን እንችላለን ማወዳደር።

አይተገብርም ምንም ሆን ብሎ፣ እነተኛ የዴ ተከታይ፣

አላማ ሳይኖረው፣ ይውላል ባለመተግበር ላይ፣

ቢሆንም፣ ሳይሰራ አያሳድርም አስፈላጊውን ስራ።

ከልብ በመነጨ ታላቅ ሰብዓዊነትን ይፈጽማል —

የሰዎችን ምስጋና ፈልጋ ሳይሆን።

የፍትህ ትልቁ ስራ ህግጋትን በማንኛው መንገድ ማስረጽ

እና ሁሉንም ከተቀመጠው አንጻር ማየትን ነው።

ታላላቅ የተባሉ አመለካከቶች ሥራችንን፣ ወደ ወግ ወጥመድ ውስጥ ያስገቡብናል፣

ይህንን ወግ በፍላጎታቸው የማይቀበሉትንም፣ ያስገድዷቸዋል።

ይኧው፣ እንደምናየው፣ ዳውን ስናጣው ዴ ይቀረናል፣

ዴን ስናጣው ደግሞ፣ ተስፋ የምናደርገው በሰብዓዊነት ላይ ነው፣

መልካም ምግባር ሲጠፋ፣ ህግ ገና ይከበራል በየቦታው፣

እና ህግን ሲጠፋ ደግሞ ወገኝተኝነት ብቻ ይቀራል።

ወግ — የባዶነት ዕምነት መሸፈኛ ነው፦

ሃሳብ በብዥታ ይጠፋል።

በውስጡ የመሃይምነትና ድንቁርና ውልደት

እና የግርግርን ቅርበትን ያበስራሉ።

ስለዚህ ጠቢብ፣ ከጥራዝነጠቅነት ይዘትን ይመርጣል፣

አበባውን ሳይሆን ፍሬውን ያስቀድማል።

39

ለዘመናት የኖረ ሁሉ፣ ወደ አንድነት ለመምጣት ይጥራል፦

ይጥራል ሰማይ የጠራና ብሩህ ለመሆን፣

መሬት በራሱ ጥንካሬና ቋሚነት ይኮራል፣

ውሃ በተቀደደ ቦይ ሞልቶ እንደወንዝ ይፈሳል፣

እና ህይወት ያለው ትውልድ ሁሉ፣ አዲስ ለመውለድ አይደክመውም።

የመንግስቱን አንድነት ይጠብቃል፣ ንጉስ እንዲሁም፣

በራሱ መልካም ምግባር፣ ይሆናል ምሳሌ ለዜጎቹም።

አንድነትን ማጣት ሁልጊዜ አደጋ ላይ ይጥላል፦

ልክ እንደ ሰማይ በጥቁር ደመና መብረቅ ተሰንጥቆ እንደሚቆራርጥ፣

ሊሰነጠቅ ይችላል መሬትም፣በመሬት መንቀጥቀጥ፣

ይለወጣል ባዶ ቦይ ደርቆ ወደ በረሃነት፣

እንዲሁም ይጠፋል ተፈጥሮ ማንኛውም ዓይነት፣

ለሚቀጥለው ትውልድ ካልሰጠ ህይወት።

እንዲሁም ንጉስ የህዝቡ ሁሉ የመካምነት ዓርአያ ካልሆነ፣

በመውደቅ አደጋ ላይ ይገኛል አገዛዙ፣

ትንሹ ለትልቁ ድጋፍ እንደሚሆነው ሁሉ፣

ህዝብ በድጋፉ ስልጣን ያጠናክራል ማንኛውንም፣

እና ያስፈልገዋል ደግሞ ለማክበር ምክንያትም።

ንጉሥ እራሱን በራሱ “እንደተራ” እና የማይረባ” ብሎ ከቆጠረ

ምናልባት ከህዝቡም ድጋፍ እና ሃዘኔታ

በዚህ መልኩ አላገኝም ብሎ ይገመታል።

ነገር ግን ይህ ሊደርስበት የሚችል የተሳሳተ መንገድ ነው፣

አደገኝነቱ በህዝቦቹ አይን ክብሩን ሊያሳጣው ይችላል።

አስተውል፣ ከተፈታታ የጋሪን ጎማ፣

አይቻልም መጠቀም እቃዎቹን ለየብቻቸው፣

ወጥ ሲሆን ብቻ ነው ጠቃሚ የሚሆነው፣ አንድ እቃ በእራሱው፣

እና ከሌሎች እቃዎች ጋርም ነው በትክክል ሲገጥም።

ስለዚህ በጥርጣሬ ውስጥ መውደቅ ባያስፈልግም፣

መገመት አያሻም ራስን እንደ ከበር ድንጋይ፣

ነገር ግን አያስፈልግም መቁጠር ደግሞ አድርጎ አለትም።

40

የዳው እንቅስቃሴ — ካለመቀበል ነው፣

በድክመት — የአዙሪት ማሽከርከሪያ አንቀሳቃሽ ነው፣

ከመሆን — የሁሉ ነገር ውልደት።

የመሆን ራሱ መከሰት —

መኖርን ካለመቀበል ነው።

41

ብልህ፣ ስለዳው አውቆ፣ እንደሱ ለመሆን ያለመታከት ይደክማል፣

ተራ ሰው አንዳንዴ ይነሳሳል፣ አንዳንዴ ይተወዋል፣

ሞኝ ደግሞ ዳውን ለስላቅ ይዳርገዋል።

ነገር ግን፣ ቢሆንም፣ ያለስላቅ ዳው ዳውን ባልነበር፣ ያለጥርጥር።

ያለምክንያት አይደለም እንዲህ የሚባለው፣ ለነገሩ እብድ ብዙ ያውቃል፣

ትክክለኛ መንገድ የያዘ — ልክ መንገዱን የሳተ አድርጎ ያስባል፣

ከፍተኛ የመንፈስ እርካታ ላይ የደረሰ — ልክ አንደ ወደቀ፣

ንጹህ ልቦና ያለው በሌሎች ዓይን — ልክ እንደ ወረደ።

እንደዚህ አይነት ምሳሌዎችን ብዙ መጥቀስ ይቻላል፦

ሁሉ ነገር ሲሟላ በሌሎች ዓይን የጎዶሎነት ስሜት ይፈጥራል —

ስንት ጊዜ በጎአድራጊዎችን እንደ አጭበርባሪ ተቆጥረዋል!

በተለዋዋጭ አለም እውነተኛ ሃቅን ማግኘት አስቸጋሪ ነው።

ታላቅነት፣ ከተራ እውቀት ወሰን በላይ ነው:

አይቻልም የታላቅን አራት ማዕዘንን ማዕዘኖች ማመልከት፣

ውድ ስጦታዎችን፣ ለረጅ ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋል፣

ኃይለኛ ጩኸትን፣ ለመስማት ያዳግታል።

የታላቁን ዳው ምንነት፣ ትክክለኛ ገለጻ የለውም፣

ስያሜ የለውም ከዓይን የተሰወረ ነው —

እና ቢሆንም ዳው ይፈጥራል የዓለምን መጀመሪያ፣

እና ሁሉ ሂደቶች ወደሱ ይወስዳሉ በመጨረሻ።

42

ዳው ውህደት ነው — በውስጡ የዓለምን አንድነት መገንዘብ ነው፣

በአንድነት ውስጥ እያንዳንዱን ነገር ስናየው

በውስጡ ሁለት እርስ በእርሳቸው ሊገናኙ የማይችሉ ጥረቶችን እናያለን።

እነዚ ሁለት እንደሰማይና ምድር የተራራቁ ጥረቶችን በየጊዜው ይተላለፋሉ፣

እና፣ ማለትም፣ ሦስተኛ ኃይል አለ፣

ይህ ምን አይነት አዲስ ኃይል ይፈጥራል።

እነዚ ሶስቱ የመኖርን እስትንፋስ ይወስናሉ

እና የሁሉንም ነገሮች አፈጣጠር።

እያንዳንዱ ፍጥረት በውስጡ ኢን ወይም ያንን ያቀፋል —

በህይወት ኃይል አማካይነት ፂን የሁለቱን ውህደት ይፈጥራል።

ሁሉም ሰዎች መከራና ስቃይ ያሳልፋሉ፣

ግን በሌሎች ዓይን ደስተኛ እንደሆኑ ለመምሰል ይሞክራሉ፣

እድለቢስ መባልን አይወዱም፣

ነገር ግን፣ ገዢዎች አላቸው እድልም ሀብትም፣

ሆን ብለው ግን እራሳቸውን “ምስኪን” እና “ድሃ” አድርገው ይቆጥራሉ።

እንደዚህ ትንሹ ትልቅ ለመባል ይጥራል፣

ትልቁ እራሱን ዝቅ ለማድረግ ይሞክራል፣

በኃይል ከፍተኛ ቦታ የደረሰ ሰው

በራሱ ላይ ኃይል እንዳይጠቀሙበት ይፈራል፣

የህይወት ፈተና ብዙ ያስተምራል፣

በሌላ በኩልም ህይወት የሆነ ነገር ታገኛለች ከእኔም።

የትምህርቴ ቅመም — እራሴን ነጸብራቅ ማድረግ።

43

ይቅር ማለት — ከባድ መከራን ያሳልፋል፣

ቁሳ ቁስ የሌለው —

ምንም ነገር ወደሌለበት ባዶነት ውስጥ ይገባል።

ብልህ፣ ይህን የሚገነዘብ ነው፣ምንም ሳይተገብር ጥቅም —

ና እውቀትን — ከትምህርት በቃላት ያልተሸፈነ ያገኛል

ነገር ግን የተወሰኑት ብቻ ይህን ሃቅ እንደ የህይወት መርህ ይቀበሉታል።

44

የትኛው ነው ለሰውነት የሚቀርበው — ስም ወይስ ህይወት?

ላንተ ውዱ ምንድን ነው — ህይወት ወይስ ማግኘት?

እውነት አይደለም እንዴ፣ አንዳንዴ ማግኘት ከባድ ነው፣ እጦትን ከማወቅ?

ሰፊ ሃብትና ዝና ሲኖር፣ የማጣት እድሉ የበለጠ ይሆናል፣

ህይወት በትኩስ ስሜት የተሞላች ከሆነ፣ የበለጠ ዋጋ ያስከፍላል፣

መጠኑን የሚያውቅ ብቻ ፣ ኀፍረትና መከራን ያርቃል፣

እና ህይወቱን ለረጅም ጊዜ ያራዝማል።

45

በተወጠረ ሸራ ላይ ያለ፣ የሚያምር የቅዱሳን ስዕል እንከን የሌለው ይመላል፣

ማለቂያ ከሌለው ባዶነት ጋር በሚገናኝበት ጊዜ፣ እራሱ ሸራው፣

ተራ እና የሆነ ነገር ይመስለናል፣ ታላቅ ጥበብ የነበረው።

ግልጽ ያልሆነ ንግግርም ይጥራል ለመሆን በጣም ትክክል፣

እና በሌላ መልክ ዕይታ — እውነተኛ ታላቅ ውበት።

የታወቀ ነው፣ እንደሚያሸንፍ እንቅስቃሴ ብርድን፣

በትዕግስት ይታለፋል የፀሃይ ቃጠሎም።

ህይወት የተወሳሰበ እና የሚያሳስብ ምስጢር በምታቀርብልን ጊዜ፣

ትግስትና የሃሳብ ብሩህነት ይህን እንድንገነዘብ ሁል ጊዜ ይረዱናል።

46

ዳውን፣ በአመራሩ ላይ ቢያውለው ኖሮ መንግስት፣

ፈረሶች በሰላም ያዳብሩ ነበር በፋንዲያቸው መሬት፣

ዳውን በሃገሩ እና በመንፈስ ከረሱት፣

የጦር ፈረሶች በሜዳ ላይ ያስካካሉ።

ያልተገራ ስሜት፣ ከተፈጥሮ አደጋ የባሰ ነው፣

የማግኘት ጥማት፣ ከማንኛውም ዓይነት ማጣት የበለጠ ያጠፋል።

ከማእበል የከፋ ጥፋት፣ በቃኝን አለማወቅ ነው፣

ዘላለማዊ ደስታ ማግኘት የሚችለው፣ ትርፍን የማይፈልግ ብቻ ነው፣

መጠቀም ከሚያስፈልገው በላይ።

47

ዓለምን ለማወቅ ብዙ እርቆ መሄድ አያስፈልግም።

ረጅም መንገድ በሄድን ቁጥር ትንሽ እናውቃለን።

ብልህ፣ በመስኮት ሳያይ፣ የሰማይን መንገድ ይመለከታል፣

መልክ ማየት አያስፈልገውም፣ ትክክለኛ ስም ለመስጠት።

ምንም ሳይተገብር አስፈላጊውን ነገር ይፈጽማል።

48

የሚማር ሰው — የእውቀት ሃብትን ያካብታል።

ዳውን የሚከተል ሰው፣ ሆን ብሎ በየቀኑ ይጥላል፣

የመተግበር አስፈላጊነት መጥፋት እስኪጀምር ድረስ —

እንዲሁ ጠቢብ ምንም አለማድረግ ላይ ይደርሳል።

ትክክለኛ አለመተግበር ያልተሰራ ስራን ለነገ አለማስቀረት ነው።

የማይተገብር፣ ኃይል ሳይጠቀም ውጫዊ አለምን ያሸንፋል፣

ግን የራስን ፍላጎት በሌላው ላይ መጫን መሞከር ዋጋ የለውም።

49

ጠቢብ ሰው በመንፈሱ የሚቀያየር ጸባይ አይገኝበትም —

መንፈሱን የሚያበለጽገው ከሚገናኛቸው ሰዎች ጋር በሚያደርገው ንግግር ነው።

ደጋጎችን ሳይለወጥ በደግነት ይቀበላል —

ለክፋትም ቢሆን በደግነት ይመልሳል

በዚህ መልኩ ደግነትን በራሱ ውስጥ ፍጹማዊ ለማድረግ ይጥራል።

እምነት የሚያሳድር ሰውን ያምናል፣

የሚያስመስሉትንም ቢሆን በማመን ይቀበላል —

በዚሁ የመንፈስ ንጽህናውን ያበለጽጋል።

ከሰዎች መንፈስ እንቁውንም ቆሻሻውንም ይሰበስባል፣

ክፉውንም ደጉንም ሳይለይ።

ህይወትን እንደ ህጻን ልጅ ይቀበላል

ሳይፈርድ ሳይመርጥ፣

ሁሉንም በአንድ ላይ በዴ ያቀልጠዋል።

50

ወደ ዓለም ስንወለድ እንመጣለን፣

በሞት ደግሞ ወደኋላ እንመለሳለን።

ከአስር ሰዎች ሶስቱ ብቻ — በብልጽግና ላይ ይገኛሉ፣

እና ሶስቱ ከህይወት ፍጻሜ ደረጃ ላይ ቆመዋል፣

የተቀሩት ደግሞ በህይወት ፍጻሜ ላይ በመሆን

የሞትን ቅርበት ብቻ ያፋጥናሉ፣

እና በዚህም ምክንያት በጣም ለመኖር ይፈልጋሉ።

ነገር ግን ሰዎች እንደሚሉት፣

የህይወትን ጫፍ በትክክል የሚታወቀው፣

ህይወትን ያወቀ ሰው፣ ከተናካሽ አውሬዎች፣

ከጦረኞች የጦር ጥቃት መዳን ሲችል ነው።

ከነብር ጥፍር፣ ከጎሽ ቀንድ

በውስጡ ለሌላ አማራጭ ቦታ የለውም፣

ስለዚህ ተናካሹም ጥርሱን ወዴትም ማስገባት አይችልም፣

ሞትም ወደሱ ለመቅረብ መሰረት የለውም።

51

ዳው ሁሉንም ሲፈጥር አይደክመውም።

የዴ ምንነት በመስጠት ላይ ነው የተመሰረተው

ለሁሉም ለነሱ ምግብና እንክብካቤ።

በቁሳዊነት፣ የሁሉም ቁስ ነገሮች የመሰረት መሰረት ነው፦

በእድገት ላይ

ምናልባት ፍጹማዊነት ላይ ይደርሳል።

ለዚህ ነው መላው ዓለም ዳውን ለመከተል ዝግጁ የሆነው፣

እና የዴ ማንኛውም ነገር እንዲሁ እንድታከብረው ያስገድድሃል

በትእዛዝ ወይም በግዴታ አይደል

ምክንያቱም የነገሮች የተፈጥሮ ሂደት እንደዚህ ነውና

ዳው የሚፈጥረውን ሁሉ፣

ዴ እሱን በመከተል ያቀማጥላል፣ ይንከባከባል፣ ይጠብቃል፣

እና ከጠላቶችም ይከላከላል።

ሳይኖረው፣ ያደርጋል፣

ይፈጥራል፣ ግን በፈጠረው አይኩራራም፣

መግዛት ሳይሆን፣ መምራት —

እነዚህን መርሆዎች መከተል አለበት

ወደ ዴ የሚጥር ማንኛውም ሰው።

52

ማንኛው ነገር አመጣጥ አለው፣

እንደምክንያት ልንቆጥረው የምንችለው።

ምክንያቱን አውቀን፣ በውጤቶቻቸው ስራዎቻቸውን ማግኘት ያስፈልገናል፣

ውጤቱን አውቆ ስለ ምክንያቱ መርሳት አያስፈልግም —

የዚያን ጊዜ ከአደጋ ሁልጊዜ ማምለጥ ትችላለህ።

ሁሉም ያውቁታል፣ ለምሳሌ ስሜት ይቀዘቅዛል፣

ከዓለም በሩን ዘግቶ፣

ማንኛውም ሰው ህይወቱን በሙሉ ያለችግር መኖር ይችላል፣

ግን ለስሜትና ግንፍልተኝነት ከተገዛን፣

በራስ ኃላፊነት መውሰድ ነው፣ በጭንቀት ለመተብተብ፣

ከችግር ምንም እስክትሞት የሚያድንህ የለም።

ብሩህ ሃሳብ የማይታዩ ዝርዝር ነገሮችን ለማየት ይረዳል፣

የኃሳቦች ኃይል ካለህ፣ ሊያመልጡህ የደረሱትን ትይዛቸዋለህ።

ተፈጥሮን በመገንዘብ፣ የአዕምሮ ብርሃን ተጠቀም —

እራስ ለራስ ትመልሰዋለህ በግልጽ በመረዳት

የዓለም አንድነትንና የክፍሎቹን የእርስ በእርስ ተጽዕኖ፣

እራስህም፣ ሰዎችም ላይ፣ ጥፋት ልትፈጽም አትችልም።

ይህንን ነው ሰዎች “ጽኑ መሆን” የሚሉት።

53

ጥረት ወደ እውቀትና ታላቁ መንገድ ይወስዳል፣

ጉዞውን በሱ የጀመረ፣ መንገዱን አይስትም፣

ሊፈራ የሚችለው አሁን ከመንገድ እራሱ የታጠፈ ሰው ነው —

የዳው መንገድ ሰፊና ቀጥተኛ ነው ወደፊት ይወስዳል አይጠማዘዝም፣

ግን ሰዎች ብዙ ጊዜ ጠባብ የእግር መንገድ ይመርጣሉ።

ገዢዎች በሚያማምሩ ቤቶች ውስጥ ሆነው

በቅብርርና እየኖሩ አያስተውሉም፣

የሃገሩን ሜዳ የጥለቀልቁታል በአረም ፣

እና ለህዝቡ ዳቦ አይበቃውም።

ሃብት ያካበቱ እና ወርቅ አንገታቸው ላይ ያጠለቁ፣

በተለያዩ የብልግና ስራዎች ናቸው የተጨማለቁ፣

ያለምክንያት አይደለም ህዝቡ ንቀት የሚያሳድርባቸው፦

ጉረኛና ሌባ ብለው ይጠሯቸዋል —

ዳው የዚህ አይነቱን ስራ ይቃረናል።

54

ለዘመናት፣ የቆመ አጥርን፣ ለማፍረስ ቀላል አይደለም።

የቤተሰብ ትስስር፣ በመላመድ ከጠነከረ፣ ከባድ ነው ከዚያ ለማምለጥ —

ልጆች ሁልጊዜ አባቶቻቸውን ያከብራሉ፣ ባህሉን በማጠንከር።

በትክክል እውነተኛ ዴን ማግኘት ያለበት፣

እራስ በራሱን ፍጹም ለማድረግ የሚጥር ሰው ነው።

ከተማውን ለማሻሻል የሚደክም፣ ዴን የበለጠ ያገኘ ነው።

ፍሬማ ዴ ያለው፣ ለሃገሩ የሚሰራ ሰው ነው።

ዴን ለማግኘት የሚደክም፣ ዓለምን ለማሻሻል የማይታክት ሰው ነው።

ግን የሆነ ነገር ለማሻሻል በምትሞክርበት ጊዜ፣

ማንን መንከባከብ እንዳለብህ በሰፊው ማወቅ ትችላለህ።

ወደ ችሎታህ ጫፍ ለመድረስ ስትጥር —

በታላቅ ስሜት በራስህ ውስጥ ታያለህ።

ፍጹም የሆነ የቤተሠብ ግንኙነት፣ ቤተሰብን በሌላ አይን ትመለከታለህ።

አገርና ከተማህን ለማሻሻል ስትባዝን፣

የበለጠ ችግራቸውን መፍታት ትችላለህ።

ዓለምን ለማሻሻል ስትጥር፣ ሁሉንም ታውቃለህ በዚህ ምድር።

በዚህ ምክንያት ብቻ አውቃለሁ የዓለምን ምንነት፣

እራሴ ይህን መንገድ ሁሉ ስላለፍኩበት።

55

ዴን ያገኘ እንደ ጨቅላ ህጻን ነው።

ዓለም ሁልጊዜ ልጅን ይባርካል፣

እና የዱር አራዊቶችና ወፎች እሱን በደመነፍስ ይጠብቁታል —

ትንሽና ደካማ ቢሆንም፣ በተወሰነ ሁኔታም ቢሆን ይኖራል።

ህጻን፣ የውስጣዊ መርህ ምሳሌ ነው፣

ገና የሁለት ጾታ ውህደት ምስጢር ሳያውቅ።

ቀኑ ሙሉ ይጮሃል ድካም ሳይሰማው —

ከዓለሙ ጋር በሰላምና ስምምነት ይኖራል።

ለጠቢብ፣ ሰላምና ስምምነት ማለት ጽናትን መጠበቅ ነው፣

ጽኑነትን ማወቅ ማለት የአእምሮ ብሩህ መሆን ነው።

ህይወት፣ በሃሳብና ጉዞ የተሞላች ናት፣

ወደ ስኬትና ብልጽግና ጉዞ፣ ጊዚያዊ ደስታን ይሰጣል፣

ግን የበለጠ ጉልበት ማጥፋትን ይጠይቃል።

ጊዜያዊ ጉዞ እንዴትም ጥሩ አይደለም፣

ከዴ ጋር ምንም ግኑኝነት የለውም።

ቶ ሎ በቁንጅና ማበብ ወደ ፈጣን መጠውለግ ይወስዳል —

ዳውን አለመከተል የሞትን ቅርበት ያፋጥናል።

56

የሚያውቅ ሰው — ለማብራራት አይጥርም።

የሚያብራራ —

ራሱ አይገባውም።

መቼ ስሜትህን ማብረድ ትችላለህ?

ከውጩ ዓለም ፊት በሮችህን ስትዘጋ፣

እና ከማንኛውም ዓይነት ትስስር ነፃ ስትሆን፣

እና ግንፍልተኝነትህን ስታደነዝዝ፣

በህይወት በብልጭታ ቦታ እኩል የሆነ ብርሃንን በህይወትህ ስታገኝ፣

ባዶ የሆነ አሰልቺ አስተሳሰብን ስታስወግድ —

ከዓለምጋር ሚስጥራዊ ውህደት ታደርጋለህ።

ጠቢብ፡ ከዚህ ላይ የደረሰ፣ ለማንም ጠላት አይደለም፣ ወዳጅም አይደለም፣

ከማንም ጋር ቅርበት የለውም እና ማንንም አያርቅም፣

ደግ ነገር አያደርግም እናም ክፋት አይፈጽምም፣።

ለንቀትም ሆነ ለክብር ግዴለሽ ነው

ለማጣትም ሆነ ለማግኘትም

ቁሳዊ ሃብት

እና መላው ዓለም በክብር ያየዋል።

57

አገርን በተቀመጠው ደንብ መሰረት ያስተዳድራሉ፣

በጦርነት ላይ ያልተለመደ ነገር መፈጸም ድል ለማድረግ ይረዳል፣

ግን መላውን ዓለም በስሩ ማድረግ የሚችለው

ባለመተግበር ላይ ያለ ሰው ብቻ ነው።

በእርግጥም የተለያዩ የሚከለክሉ ደንቦችን ማብዛት ይቻላል

ብዙ ጊዜ ግን ድህነትን ያስፋፋል።

ገዢዎች እነዚህን ደንቦች በጠበቋቸው ቁጥር በኃይል፣

የበለጠ የመሳሪያ ቁጥር እየጨመረ ይመጣል

እና በሃገሪቷ ላይ ግርግርን ያቃርባል።

ትምህርት የሚከተሉትሉትን ነገሮች ያመጣል

አዳዲስ አደገኛ ነገሮችን መፈጠር፣

የደንቦች ቁጥር እየበዛ ና እያማረረ ሲመጣ

ወንጀልም የበለጠ እየተስፋፋ ይሄዳል።

ለዚህ ነው ጠቢብ መሪ እንደዚህ የሚያስበው፣

ካልተጠበቀ ውሳኔ መቆጠብ እንዳለበት፣

ሁሉም የተሻለ የሚሆነው ራሱ ሲለወጥ ነው።

የተበለሻሹ ነገሮች ሁሉ እራሳቸው ወደመስተካከል ያመዝናሉ፣

ስልጣንን የጨበጠ መረጋጋትን ሲያሰፍን።

እና ሰዎች የበለጠ የመበልጸ እድል ይኖራቸዋል፣

መንግስት የማይረብሻቸው ከሆነ።

ንጉስ የራሱን ፍላጎት እና ስሜት ከገራ፣

ህዝቦቹ ተፈጥሮ ወደለገሰቸቸው ሰላማዊ ኑሮዋቸው ይመለሳሉ።

58

በደግ መንግስት ዘመን ዜጎችም የዋህ ይሆናሉ፣

በኃይለኛ መንግስት ጊዜ ግን፣ ሰዎች በህግ ወጥ መንገድ መበልጸግ የተካኑ ይሆናሉ።

በእድለቢስነት ውስጥ እድለኝነት ይወለዳል፣

በስኬት ስር መከራዎች ይደበቃሉ —

ማለቂያ የሌለው የነሱ አዙሪት ወዴት ይወስዳል?

ትክክለኛ የነበር ሁሉ መበላሸቱ አይቀርም፣

ደግ የነበር ሁሉ ወደ እርግማን መለወጡ አይቀርም፣

እና የሰው ግራ መጋባት — ዘላለማዊ ነው።

ስለዚህ ብልህ መሪ ጠንካራ ነው፣ ግን ክፉ አይደለም፣

ግልጽና ቀጥተኛ ነው ግን፣ የሰዎች ድክመት ይገነዘባል፣

ወግ አጥባቂ ነው፣ ግን ከትግስት የራቀ አይደለም፣

ለአላማው ጽኑ ነው፣ ግን አላስፈላጊ ዋጋ በመክፈል አይደለም፣

እና የእውቀት ብርሃን ዓይኑን አይጋርደውም።

59

ሰዎችን ከተፈጥሮ ህግ ጋር አስማምቶ ለመምራት፣

ገዢ ሁልጊዜ ምግባሩ ቁጥብ መሆን አለበት፣

ተቃራኒ የሆኑ ውጤቶች ሊመጡ እንደሚችሉ በመገመት፣

አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዳያመጡ ቀድሞ በማየት፣

የራሱን ዴ ለመላው አለም ማበራከት አለበት።

እንዲህ ከሆነ

ተቃውሞ በሱ ሃሳብ ላይ አይችልም ሊነሳበት።

ያ ስልጣን፣ ውጫዊ የሚገድበው ኃይል ሊኖር አይችልም፣

ሚዛናዊ የሆነ እና ከወገንተኝነት የጸዳ አቋሙን መጠበቅ እስከቻለ ድረስ።

በመንግስትና በወላጅእናት መሃል መመሳሰል አለ፦

አሰባስቦ በአንድ ላይ ያጠናክራል የተበታተኑ ሰዎችን፣

እና ዓላማው — ማስወገድ ነው የይስሙላ አንድነትን።

ገዢ ይህን ሲረዳ፣

እንደ ወላጅ እናት ኃላፊነትን በጀርባው ይሸከማል —

በዚያን ጊዜ ጠንካራ መሰረት ያለውና ስር የሰደደ ስልጣን ይኖረዋል፣

የዓለምን ህይወት መቀጠልና የወደፊቱን አርቆ ማየት ይችላል።

60

ከትንሽ ዓሳ ጣፋጭ ምግብ ለማዘጋጀት

ከፍተኛ ድካምና ትግስት ይጠይቃል —

ይህ ሃቅ ደግሞ

ከመንግስት አስተዳደር ጋር ቀጥተኛ ግኑኝነት አለው።

ገዢ በአመራሩ ዳውን ለመከተል ከጣረ

የችኮላ መንፈስ፣ ትግስት ማጣትና የተለያዩ ጥቃቅን ጉድለቶች

በስራው ላይ ሊረብሹት አይችሉም።

እሱም ሁልጊዜ ዜጎቹን በክፋት አያስባቸውም —

ዴ ያያይዛቸዋል የተበራከተ ትስስር እንዲኖራቸው።

61

የታወቀ ነው “መንገዶች ሁሉ ወደሮም ያመራሉ”፦

ኃያል ሃገር የመጠራቀሚያ ቦታ ነው።

ልክ የተለያዩ ጅረቶች ተሰባስበው ወደ አንድ ወንዝ ፈሰው፣

እና እነዚህ ወንዞች ያመራሉ ወደ ውቅያኖስ አንድነት ፈጥረው።

እንደዚሁም ሰዎች በተለያዩ ፍላጎቶች ተመርተው፣

በኃያል ሃገር መሰባሰቢያ ማዕከል አግኝተው፣

እዚያ አንድ ወጥ ህብረት ይፈጥራሉ ተሰባስበው።

ለኃያል ሃገረ ልክ እንደሚስት መታገስ ዋጋ አለው፦

በመገንዘብ የውጭ ቁንጅናን ኃይልን፣

የባል የበላይነት፣ አሸንፋ ታዛዥ በመሆን፣

በትግስት የበላይነትን በመዋጥ —

ሁልጊዜ ድል የምታደርገው እሷ ነች።

ኃያል ሃገርም የተቸገረ ትንሽ ጎረቤት ሃገሩን በተመለከተ

መታገስ ብቻ በቂ ነው

ሳይታሰብ ጎረቤቱን ለበዋጥ፣

ትንሻ ሃገር ለትልቁ ወራሪ ይህንን ሲተውለት፣

እንዲውጠው በመታገስ ሲፈቅድለት፣

በዚህ ሁኔታ

አዲስ ሃብት ከአሮጌው ጋር የማጣመር ዕድል ያገኛል።

ወጣም ወረደ፣ እንዲህ በዚህ ውጤት ኃያል ሃገር ይፈጠራል።

መዋሃድ ለሁሉም ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል፦

ትልቋ ሃገር የበለጠ ዜጎች ይኖሯታል፣

የትንሿ ሃገር ሰዎች፣ ያገኛሉ ከዚህ ቀደም አይተውት የማያቁት ዕድል።

እንዲህ ሁለቱም እንደፈለጉት ያገኛሉ።

መታገስ — ወደ ታላቅ መሆን ያመራል።

62

ዳው የምስጢራው ምንነት መከሰትን ይመሰላል —

የደግነት እንቁ፣ ደግነት — በሌለበት ድጋፍ ያገኛል።

ማን ዋጋ ይሰጥ ነበር ለመልካም ቃላት

እና ለጨዋ ሰው ድንቅ ስራ፣

ለማነጻጸር ያህል

በራስ በውስጥ ክፋትን ካላየ?

ከሚያምር የቤተመንግስት መውጫ በኋላ

ሹማምንቶችን በማስተዋል፣

አይደለም ወይ የምታከብረው የበለጠ ጠቢቡን፣

በጨዋነት እየኖረ ያገኘው ዳውን?

ለዚህ አይደለም ወይ የድሮ ሰዎች ዳውን የሚያከብሩት

በሱ ውስጥ የልቦና መጠን እውነታን ነውን አግኝተውበት?

ሃብትን ለማካበት ሳይጥሩ፣

እነሱ ፍጹም አለመሆናቸውን ተገንዝበው

እና ኃይል ሳይጠቀሙ ለመፍታት ሞክረዋል —

በዚህ መልኩ ዳውን ሰማይ አድርሰውታል።

63

ጠብቅ አለመተግበርን፣ የመንፈስ ሰላምን ለማግኘት፣

ጣዕምን አጣጥም ጣዕም ከሌለው ስራ፣

ብዙ ባልሆነ ነገር ውስጥ ብዙ አግኝ፣ እንደትልቅ ቆጥረህ ትንሹን፣

እና በዴ እርጋታ መልስ ለቁጡ እርግማን።

ከባድ ስራን ተያያዝ ገና ከጅምሩ፣

ታላቅ ነገር ጀምር ከትንንሽ ቡቃያዎች።

ከተራ ችግር አይደለም ወይ ትልቅ ችግር የሚፈጠረው፣

ትልቅ ጉዞ የሚጀምረው ከትንሽ እርምጃ ነው።

ጠቢብ ትልቅ እቅድ አያቅድም፣

ስለዚህ ታላቅ ነገር በዚሁ ይፈጥራል።

ቶሎ ማንኛውንም ጉዳይ ለመፈጸም የሚስማማ፣ በአብዛኛው አያደርገውም፣

ቀላል መንገድ ብቻ የሚመርጥ ችግር ያጋጥመዋል —

ግን ብልህ ከማንኛውም አይነት ውጥን ውጤት ይጠብቃል፣

ስለዚህ መፍትሄ የሌላቸው ችግሮች አያጋጥሙትም።

64

የማንቀሳቀስ ነገርን፣ ዝም ብሎ የራስ ማድረግ፣

የማይወስንን ሰው — በቀላሉ መመደብ ይቻላል፣

ጠንካራ ያልሆነን ነገር፣ ወደአፈርነት መቀየር ከባድ አይደለም፣

ትንሽ የሆነን ደግሞ መቆራረጥ ይቻላል።

ገና ሊፈነዳ ያቆጠቆጠ ነገር ላይ፣ ትኩረት ስጥ፣

ቀደም ብለህ አስከብር ስርዓት፣

የግርግር ጭላንጭል ከመታየቱ በፊት።

ከዋርካ ተክል ከሁለት እቅፍ በላይ የሆነ ግንድ ያድጋል፣

ትልቅ ማማ ከአፈር ክምችት ይጀምራል፣

እና በብዙ በመቶውቹ የሚቆጠር መንገድ

ከእግርህ ስር ይነሳል።

ፈጣን ሰው ነገር — ያበላሻል፣ ራስወዳድ — ያጣል፣

የቸኮለ — የውጤት ጫፍ ላይ ሲደርስ፣ ሽንፈት ይጠብቀዋል።

ብልህ ምንም ነገር አያደርግም ስለዚህ እና ስለዚህ ስኬማ አለመሆን አይችልም።

እሱ፣ሳይኖረው፣ ሳያጣ እና ሃብታም ለመሆን አይጥርም።

በስራው መጨረሻ ላይ፣ ልክ እንደ መጀመርያው፣ ጥንቃቄ ያደርጋል፣

እና ስራውን በስኬት ይጨርሳል።

የአለመፈለግን ጥበብ ያልማል፣

ዋጋ አይሰጠውም፣ አብዛኛው ዋጋ ለሚሰጠው፣

መረዳት ከሚቻለው በላይ ያለን ይማራል

ሰዎች ግምት ሳይሰጡት፣ ወደሚተውት ነገር ይመለሳል።

ሁሉም እቃዎች የራሳቸው ብቸኛ የሆነ ተፈጥሮ አላቸው፣

ስለዚህ በነሱ ላይ ተጽዕን ለማሳደር አይደፍርም።

65

በጥንት ዘመን፣ እነዚያ ፍጹማዊ ዳውን ያወቁ፣

ተራ ሰዎችን ለመጠበቅ ሞክረዋል

ባለስልጣኖች የሚሰሩትን እንዳያውቁ —

የአመራር ስልቱን ህዝባቸውን እንዳይረዳው አድርገዋል።

በአብዛኛው አገር የምትበዘበዘው፣

ህዝቡ ስለ ስልጣን ብዙ በሚያውቅበት ጊዜ ነው፣

በሃገር ሰላም የሚሰፍነው፣

የተትረፈረፈ ግልጽነት ያለው አመራር በማይኖርበት ጊዜ ነው።

ይህን የተፈጥሮ ህግ የሚያውቅ መሪ፣

ፍትሃዊ የአመራር ስልት በስራው ላይ ያሳያል፣

ይህን ፍጹማዊነት በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር፣

ከፍተኛውን ዴን ማወቅ ያስፈልጋል።

ዴ ማለት በስፋትና ጥልቀት ማሰብ ነው፣

በዚህ ሁሉ ይህን የተገነዘበ በተቃራኒው ማየት ይችላል፣

ስለዚህ ወደ አንድነትና ስምምነት ሁሉን ይመልሳል።

66

የሸለቆዎች ባለቤት መሆን በቻሉ ነበር ወንዞችና ባህሮች፣

ግን፣ ያልሆነበት ምክንያት፣ ለመፍሰስ ስለሚጥሩ ብቻ ነው ወደታች።

ታላቅ ቦታ ለመድረስ የሚፈልግ፣

ከታች ወደላይ ከህዝቡ ጋር መነጋገር አለበት፣

አንደኛ ለመሆን የሚፈልግ ሰው፣

ሆን ብሎ ከኋላ መሰለፍ አለበት።

ብልህ እንዲህ ሲያደርግ፣

ላይ ሲደርስ፣ ከችግር ጋር አይመሰልም፣

ከፊት እንኳንቢሆንም፣

መንገድ የሚያዘጋ አይመስልም።

በደስታ እሱን ወደፊት ይገፉታል

እና በችግራቸው አያማርሩትም።

ጠቢብ ከማንም ጋር አይታገልም፣ እና ስለዚህ

ብቁ የሆኑ ተፎካካሪዎች አይኖሩትም።

67

ማንኛውም ግኑኝነት ዘላለማዊ አይደለም።

ለማወዳደር፣ መጠን ያለውን ነገር ሁሉ፣

የመለካትን ምንነት ከጊዜ በኋላ ያጣዋል፣

ከመጠን ወደተቃራኒ ይለወጣል፦

ትንሽ የነበረው፣ ትልቅ ይሆናል፣

ትልቁን — ጊዜ ያሳንሰዋል፣

ስለዚህም ነው የዳው ታላቅነት የሚያጠራጥር የማይሆነው፣

በዚህ እውን ዓለም፣ ከሱ ጋር ምንም ነገርን ለውድድር አይቀርብም።

ግን ምንም ቢሆን፣ ሦስት ነገሮች ለኔ የተለየ ዋጋ አላቸው፦

በፍቅር ላይ ጀብደኝነት፣ ጀግንነትን የሚያጎናጽፍ፣

በምንም ብኩን አለመሆን፣ ወደ ልግስና የሚወስድ፣

እና ጨዋነት፣ ለስልጣን የሃገር መከበርን የሚያመጣ —

ሚዛናዊ ፍትህ፣ ተቃራኒ ነገሮችን ይፈጥራል።

የለጋስነት ወይም ድፍረትን ሚዛን የሚያዛባ፣

ወይም በስልጣን ስካር ጨዋነትን የሚረሳ፣

እሱን ሞት ያለጥርጥር ይጠብቀዋል።

ፍቅር ሁልጊዜ በጦርነት ድልን ያስገኛል

እና በማይደፈር ምሽግ ይከላከላል።

የሚወድን፣ ሰው — ሰማይ ይጠብቀዋል።

68

ልምድ ያለው ጦረኛ — ለውጊያ አይቸኩልም።

ኃይለኛ ተዋጊ መቼውንም ከራሱ እቅል አይወጣም።

ብልህ አርቆ አሳቢ መቼውንም ወደ ጦር ሜዳ አይገባም።

ታላቅ መሪ ሰዎችን በስሩ ለማድረግ ሲፈልግ፣

የራሱ ውርደት ፊት ከመቆም አይመለስም።

ይህ — ስጦታ ነው፣ የማሸነፍ ኃይል ሳይጠቀም፣

ይህ — ጥበብ ነው፣ መግዛት ሰዎችን ያለድካም፣

የጥንት ውኅደት፣ ነው ከላይም ከልምድም።

69

የጦርንት ጥበብ እንደሚነግረን፦ “ለመንቀሳቀሻ የምትጠቀምበትን መንገድ ጠብቅ፦

ቆሞ፣ “እንግዳን ከመጠበቅ”፣ ጠቃሚ ነው “እንግዳ” መሆን፣

ዝም ብሎ ወደፊት ከመገስገስ፣ ማፈግፈግ ጠቃሚ ነው፣

ጦር ከቦታ ወደ ቦታ ስታዘዋውር፣ እንቅስቃሴውን ደብቅ፣

ተዘጋጅ፣ ግን ዝግጅትህን አታሳይ፣

እና በባዶ ቦታ ጠላት ጦርነት እንዲጀምር አስገድደው —

ይህ ሁሉ፣ ሳትዋጋ፣ ድል የማድረጊያ መሳርያ ነው።”

ግን እንደ ደካማ ጠላት አደገኛ የለም፦

ልክ ድል ማድረግ ቀላል ሲመስልህ፣

ወድያውኑ ስለአስፈላጊ ጥንቃቄዎች ትረሳለህ —

እና ዋጋ የምትሰጠውን፣ ታጣለህ።

ጦርነት ተጀምሮ ፍልምያ ሲጧጧፍ፣

ስለዚህ የሚቆጭ፣ ያሸንፋል።

70

እንደመሰለኝ፣ ዝም ብዬ እናገራለሁ፣ እና ፍላጎቴ ግልጽ ነው —

ግን ማንም የሚረዳኝ አላገኘሁም።

ችግሩ፣ ወሬ እና ስራ — የሃሳብ ውጫዊ መግለጫ ብቻ ነው።

የነሱ ምንጭ — የመንፈስ የማይገለጽ እንቅስቃሴ ነው፣

ማንም ሰው ይህን በተለየ መልኩ በቀጥታ ለመረዳት አቅም የለውም።

ለእኛ፣ ልዩ ሁኔታው፣ ዋጋችንን ከፍ ያደርግልናል፣

በንግግር የመግባባት ችግርን ያመጣልና —

እና ብልህ በጥንቃቄ በልቡ ወርቅ ይለብሳል፣

ሰዎች ግን የማይረባውን የውጭ ልብስ ብቻ ያስተውላሉ።

71

ስለ አለማወቅህ ማወቅ — ታላቅ ችሎታ ነው።

የእውቀትን ወሰን አለማወቅ — የማገናዘብ ችግር ነው።

ችግሮችን ከመረዳት የሚመጣ መከራ ጉዳትን ይቀንሳል፦

ጠቢብ፣ የአጋጣሚ ስህተቶችን ክስተት ይረዳል፣

እና ስለዚህ መቼውንም ወደስህተት አይገባም።

72

ህዝቡን በኃይል ለማንበርከክ፣ እርምጃ ሲወስዱበት፣

በአብዛኛ ጊዜ፣ በተቃራኒው እንዲያደርግ ያስገድዱታል፦

ሰዎች ለጭቆና በንቀት ይመልሳሉ።

በፍርሃት ላይ የተመረኮዘ አመራር ካልሆነ፣

በዕውነት ትልቅ ስኬት ላይ ይደርሳል።

ብልህ መሪ፣ የስልጣንን ኃይል ተረድቶ፣

በሰፊው ለማሳየት መቼውንም አይጠቀምበትም፣

እንዲሰግዱለት መቼውንም ፍላጎት የለውም፣ የራስ በራሱን ክብር ጠብቆ፣

ከውጫዊ መብለጭለጭ፣ ፍሬያማ ስራ ያስቀድማል።

73

ፍርሃትን የማያውቅ፣ ለማድረግ የሚደፍር ሰው፣

እራሱንና ሌሎችን፣ ለሞት ይዳርጋል።

ግን ጨዋና ምስኪን ሰው ፍርኃትን የማያውቅ፣

ከሞት መዳን፣ ማዳንም ይችላል።

መልካም ሥራ ለመሥራት ነው የሚገፋፋቸው ሁለቱንም፣

ግን የሰማይን ምርጫ፣ ማንም አያውቀውም፦

ክፉም ደጉም መድረሱ እንደማይቀር፣ በዚህ ምክንያት፣

ጠቢብ፣ ለመተንበይ መቼውንም አይደፍርም።

ዕድል ያለደፋሮች ፍልሚያ ድል ታደርጋለች፣

ሳትጠራ ትመጣለ፣ ሳትናገር ትመልሳለች።

ያለ እቅድ ልዩ ወጥመድ ተዘርግቷል —

ግን በዚህ ዓለም ማንም ከእሱ አያመልጥም።

74

ሰዎችን ሞት በመንዛት፣ ማስፈራራት አስፈላጊ አይደለም፦

ደፋርን ህዝብ ማስፈራራት ዋጋ የለውም፣

ህዝቡ ሞት የሚፈራ ቢሆንም ቅሉ፣

ግን ከነሱ፣ ህግን ለመጣስ አይቀርም መሞከሩ፣

ክብርህን ላለማጣት፣ ሰዎች ባንተ ላይ ያላቸውን፣

በተግባር ማሳየት አለብህ ዛቻህን፣

ህግ የጣሱት ሰዎች፣ መግደል ይበቃል —

ይህን ለማድረግ አንተ ትደፍራለህ ወይ?

ሁልጊዜ፣ ውሳኔ የሚሰጥ ሰው አለ —

ዘላለሙን ፍርድ እራሱ የራሱን ይሰጣል

እራሱ ፍርዱን ያስፈጽማል።

አላዋቂ መጥረቢያ መያዙን ቢቀርበት ይሻለዋል።

ለመቅላት ሲሞክር የሞት ባለሙያ መስሎ —

እጁ ላይ ጉዳት ማድረስ ብቻ ነው ትርፉ።

75

በዘራፊ ግብር ምክንያት ህዝቡ ይራባል።

እልህ በአመራር ላይ አመጽን ይጠራል፦

ህዝቡም የሚያጣው ነገር ከሌለው፣

ለመሞት ምንም አይፈራም፣

በዚህ በዚያ ባለስልጣኖቹ ስጋውን ይበሉታል።

ገዢ ህይወቱን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ ሲያይ፣

በዚህ መልኩ የህይወቱን ዋጋ ዝቅ ያደርገዋል።

በእውነት እራሱን ከልቡ ዝቅ አድርጎ የሚያይ ብቻ፣

በአጠቃላይ ህይወት የተሻለ ነገር ሊያመጣ ይችላል።

76

ደካማ ነው ሰው፣ በህይወት እስካለ፣

የሚታለል፣ የዋህ፣ የሚጠቃ —

ግን ያ ለስላሳ ሰውነቱ

ደረቅ፣ ቀጥ ያለ፡ ጠንካራ፣ ይሆናል ሲሞት።

ሁሉ ህያው፣ ወደዚያው ነው የሚሄደው፦

በሚተጣጠፍና ለስላሳ ሰውነት፣ ህይወታቸውን ይጀምራሉ —

ግን፣ በደረቅ አጥንት ያልቃል መንገዳቸው፣

ልስላሴ — ገጽታ የህይወት፣

ድርቅ ያለ ጥንካሬ — የሞት።

ደነዝ ኃይል፣ ሃፍረት ይጠብቀዋል።

ለጠንካራ ዋርካም መጥረቢያ ተዘጋጅቷል።

ኃይለኛ፣ ጠንካራ የሆነ — ወደ ታች ይወርዳል።

ተጣጣፊ ድክመት ብቻ ያድጋል።

77

አንድ ተዋጊ፣ ቀስቱን በሚስበው ጊዜ፣

የገመዱን መሃል ሲለጥጠው በኃይል፣

እና የደጋኑን የታችኛውን ማዕዘን፣ ያደርገዋል ከፍ ወደላይ።

እየወጠረው ይሄዳል፣ ገመዱን የበለጠ በሳበው ቁጥር፣

የእጁ ውንጫፌ በሰፊው ይሆናል —

እና ይጠይቃል የበለጠ ኃይል፣ ጠንካራውን ገመዱን ለመወጠር።

እና እንዲሁ ያደርጋል ዳውም፦

ፍሬያማ በሆነ መንገድ ለመምራት ዓለምን፣

ይጥራል ትርፍ ለመቀነስ፣ ያለፈን ከመጠን፣

እጦት ሲኖር ግን ይተካል።

ዳውን የሚቃረኑት፣ የሰዎችን ልምድ ብቻ ናቸው፣

ድሃ ከሆነ ሰው ይቀማሉ፣

እንዲሁም፣ ሃብታም ለሆነ ሰው ደግሞ ይሰጣሉ።

የዳውን ግንዛቤ የተረዳ ሰው ብቻ፣

ያለውን ትርፍ፣ ከዓለም ጋር ለመካፈል ደስተኛ ነው።

ብልህ ብቻ፣ ከማንም እርዳታ አይጠብቅም።

በሰራው ስራ አይኩራራም

እና አይደክምም፣ ታዋቂነትን ለማግኘትም።

78

ምንም ነገር የለም፣ ልክ እንደ ውሃ፣ የቀጠነ እና ወደመሩት የሚመራ —

ግን ሁልጊዜ ይችላል ለማሸነፍ፣ጠንካራን የሆነን ነገር፦

ይቀበላል ማንኛውም ከውጭ የሚመጣን ግሳንግስ

ይውጠዋል ይህን ኃይል፣ ዱካውን ሳያስቀር።

ለስላሳ የሆነ ነገር፣ ማሸናፍ እንደሚችል ጠንካራን፣

ድክመት ደግሞ ይችላል መግራት ኃይልን፣

ምናልባት ይህን፣ ማንም ያውቀዋል በዓለም ላይ ያለው፣

ጥቂቱ ነው ግን የሚተገብረው።

እና ያለመታከት ጠቢብ ደጋግሞ ይናገራል፣

ጥሩ ንጉስ ማለት፣የሃገሩን ኃፍረት ሳያቅማማ የሚቀበል፣

እና የሚወስድ ማንኛውንም የመንግስት መከራ ኃላፊነትን —

እንደውሸት ይቆጥሩታል ልዩነትን፣በእውነታ ውስጥ ያለውን።

79

ቢሆንም ግዴታ መግራት፣ ቅሬታን፣

የታወቀ ነው፣ በተወሰነም ቢሆን ሃዘኔታ በውስጥ መቅረቱን፣

እና የሆነ ጊዜ ተመልሶ፣ ራስ ላይ ይደርሳል ክፋትም —

ሰዎችን በማስገደድ ጸጥ ለጥ ማድረግ፣ በራሱ መልካምነት የለውም።

ጠቢብ፣ ይመርጣል መውሰድ፣ እራሱ ኃላፊነትን፣

ይህን እንዲያደርጉ ከማስገደድ ሌሎችን።

ዋናው ቁም ነገር፣ ውልን ማክበር ነው፣ ዴንን ለሚከተል ሰው፣

ትርፍ ማግኘት፣ በሚጥርበት ቦታ፣ ሌላው።

ዳው አያዳላም እና ማንንም ከማንም አይለይም —

ግዴታውን ከሚወጣ ሰውጋ ነች፣ ዕድል ሁሌም።

80

ስለትንሽ ሃገር አልማለሁ፣

ጥቂት ነዋሪዎች ያሉባት፣ እና እርስ በእርሳቸው የሚዋደዱባት።

በኑሯቸው ናቸው በጣም ደስተኞች

ሞትን ይፈራሉ፣ አያስፈልጓቸውም ሩቅ ያሉ ሃገሮች።

ሁሉነገር አላቸው፣ አያሻቸውም ተጨማሪ ነገር ፣

ግን መሳርያዎቻቸውን፣ መጠቀም አይችሉም የትም።

እና ጀልባም፣ አላቸው ጋሪም፣

ግን ማንም በነሱ ለመጓዝ አይጥርም።

ለመረጋጋት ቢሆንም፣ የጦር መሳሪያ አላቸው፣

ግን ፍላጎት የላቸውም፣ ለመውረር ሌላውን።

ጠቢባን የፈጠሩትን ሁሉ እርግፍ አድርገው ትተው፣

ተመለሱ እንደገና፣ ወደ አያቶቻቸው ልማድ።

የሚጣፍጥ ነበር፣ ተራ ነው ምግባቸው፣

ልብሳቸው በየቤታቸው የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ቆንጆ ለነሱ ናቸው፣

ሰላማዊና በስምምነት የተሞላ ነው፣ህይወት በቤታቸው፣

በጣም አስደናቂ ነው፣ እንዲሁም ባህላቸው።

እስከ ጎረቤታቸው ሃገር አንድ እርምጃ ቢሆንም፣

መስማ እንኳን ቢቻል፣ የውሻ ጩኸትንም፣

እዚያ በኖርኩ ነበር ብዙ ዓመት፣ ከባዕድ ህዝቦች ጋር ሳልነጋገር፣

እስከዕለተ ሞቴ፣ ወዴትም ሳልመለስ ወዴትም ሳልሄድ።

81

እውነተኛ ንግግር ቆንጆ ሊሆን አይችልም፣

የሚያምሩ ቃላት አያሳምኑም።

የራስ ብቁነት፣ በክርክር አይደለም የሚገለጸው፣

የሚከራከር — ነው እውነታ የሌለው።

የተማረ አያስብል — መገንዘብ እውነታን፣

የመረጃ ብዛት — ገና እውቀት ማለት አይደለም።

አይጠቀምበትም፣ ዝም ብሎ እውቀትን የሚያካብት ሰው፣

ጠቢብ ግን በሰጠ ቁጥር፣ የበለጠ ያገኛል።

እንደ ዳው ሰማይ — ለዓለም ህይወት መስጠት፣ ጉዳት ሳያደርስ ነው፣

እንዲሁም ዳው ጠቢብ — ይፈጥራል እንጂ መቼውንም ወደ ክርክር አይገባም።

<< ïðåäûäóùàÿ çàìåòêà ñëåäóþùàÿ çàìåòêà >>
Îñòàâèòü êîììåíòàðèé